Pages

Tuesday, January 27, 2015

ማን ይናገር የነበረ ማን ያርዳ የቀበረ! – አቶ ነሲቡ ስብሃት(አሉላ)

መጽሐፍ ፍጹም ነው እምነቴ”  ቀይ ሽብርና፤ የከፍተኛ 15 እውነተኛ ታሪክ
ደራሲ፡ አቶ ነሲቡ ስብሃት(አሉላ) መስከረም 2007
አስተያየት
በአቶ ክንፈ ኪሩቤል ተስፋሚካኤል(አዲስ አበባ) ጥር 2007 ዓ.ም

Yat weldይህ የአቶ ነሲቡ ስብሃት መጽሐፍ በትክክለኛ መረጃ ላይ የተመሰረተ የስራ ውጤት ነው፡፡ በ1970 ዓ.ም “በቀይ ሽብር” ስም ያለ ፍትሕ ስርዓት ስቃይና መከራ ለተቀበሉት፤ ለአካል ጉዳተኛነት ለተዳረጉት፤ ለስነ ልቦና ጉዳት ሰለባ ለሆኑት፤ ለተሰደዱት፤ ውድ ልጆቻቸውንና ወላጆቻቸውን እስከ ፍጻሜው በሞት ላጡት ኢትዮዽያውያን ታላቅ መታሰቢያ ነው፡፡
መጽሐፉን ልዪ የሚያደርገው ስለ “ቀይ ሽብር” የተጻፈ እውነተኛ ታሪክ መሆኑ ብቻ አይደለም፡፡ በ1969-70ዎቹ የነበረውን የፖለቲካ የማህበራዊና አኮኖሚያዊ ሁኔታዎችን፤ የፀሐፊውን የግል ሕይወት፤በካዛኢንችስ በወቅቱ የነበረውን የወጣት ሁኔታ ይዳስሳል፡፡ ታሪክነቱ በአንድ የአዲስ አባበ ከተማ በከፍተኛ 15 ውስጥ የተካሄደ ቢሆንም፤ድርጊቱን በመላው የኢትዮዽያ ከተሞችና ገጠሮች “በቀይ ሽብር ይፋፋም” መፈክር ስር ወታደራዊ ደርግና በዙሪያው የተሰባሰቡ ስልጣን ፈላጊ ምሁራን በቅንብር ያካሄዱትን ዘግናኝ የግድያ ድርጊት ትዕይንታዊ በሆነ መልኩ ያሳያል፡፡
አንባቢው ሊገነዘበው የሚገባው ይህ ዕልቂት በአዲስ አበባ ብቻ ሳይሆን በመላው ኢትዮዽያ  በተመሳሳይ ሁኔታ እንደተደረገና በዚህም ከ1940-1960ዎቹ የተወለደ አንድ የኢትዮዽያ ወጣት ትውልድ በጅምላ ዕልቂት ማለፉንም ጭምር ነው፡፡
መጽሐፉ በተጨማሪ የሚዳስሰው የታመቀው የኢትዮዽያ ሕዝብ ብሶት በድንገት 1966 ዓ.ም በመቀጣጠሉ የተነሳ በወቅቱ የሕዝቡን የለውጥ ፍላጎትና ብሶት በተደራጀ የፖለቲካ አመራር ሊመራ የሚችል የፖለቲካ ፓርቲ ባለመኖሩ ወታደራዊ ደርግ መስከረም 2 ቀን 1967 ዓ.ም ስልጣን በሃይል መንጠቁንና የሕዝብን ዲሞክራሲ መብቶች መግፈፉና የግፍ አገዛዙ  የኢጣሊያን ፋሽስቶች ኢትዮዽያን በወረሩበት ዘመን ከፈጸሙት ያላነሰ  መሆኑን ያነፃፅራል፡፡
ሌላው መጽሐፉ አንባቢውን የሚያስገነዝበን የማርክሲስት  ርዕዮተ ዓለም እናራምዳለን የሚሉ ምሁራኖች በተከተሉት የፖለቲካ መስመር ልዩነቶች የተነሳ መቻቻልና መደማመጥ በመጥፋቱ በሃገሪቱና በሕዝቦቿ ላይ የደረሰውን ጥፋት ነው፡፡ በተለይ የመላው ኢትዮዽያ ሶሻሊስት ንቅናቄ(መኢሶን) የተባለ ቡድን ደርግን ወግኖ ስለመቆሙ፤ የኢትዮዽያ ሕዝቦች አብዮታዊ ፓርቲ(ኢሕአፓ) ደግሞ ደርግን ኮንኖ የራሱን አቋምና መስመር ስለመከተሉ፤ ኢሕአፓ ለኢትዮዽያ ሕዝቦች ነጻነትና እኩልነት በጽኑ ስለመቆሙና ስለመታገሉ ያስረዳል፡፡ በዚህም የተነሳ በለጋ ወጣትነት ዕድሜያቸው የኢሕአፓን መስመር በፍጹም እምታቸው የተከተሉት ወጣቶች በኢሕአወሊ ድርጅታቸው ስር ያካሄዱትን የመረረ ትግልና የተቀበሉትን መስዋዕትነት በግልጽ ያሳያል፡፡
አቶ ነሲቡ፤ የኢሕአፓን የሕዝብ ፓርቲነትን አበክረው ገልጸዋል፤ ሆኖም ትግሉ እየመረረ በሄደበት ወቅት መኢሶን፤ ወዝ ሊግ፤ ማሊሬድ፤ ኢጭአት በተባሉ የድርጅት ካድሬዎችን በመጠቀም ወታደራዊው ደርግ በቀይ ሽብር ስም ድርጅቱን የመምታቱ ሃይል በተፋፋመበት ወቅት በኢሕአፓ ድርጅት ውስጥ መከፋፈል ስለመከሰቱ፤ መዋቅሩ ስለመዘበራረቁና መፈራረሱ፤ መክዳትና ከደርግ ጋር መሰለፍን ስለማስከተሉ፤ በከተማው ትጥቅ ትግል የተነሳ ስህተቶች ሰለመፈጸማቸው በግልጽ አስቀምጠውታል፡፡ ይህም ሚዛናዊነታቸውንና እውነተኛነታቸውን ያሳያል፡፡ የሕቡዕ ድርጅታዊ አሰራር በውስጡ አለመተማመንና መከፋፈል ከተፈጠረ ጉዳቱ ቀላል እንደማይሆን ያስተምራል፡፡
ካድሬ ከፈለኝ ዓለሙ እንደ ምሳሌ ቀረቡ እንጂ፤ በአጠቃላ የደርግ ካድሬዎችን ጨካኝነት የአውሬነት ባሕሪይ በግልጽ ያሳያል፡፡ የኢትዮዽያ ሕዝቦች የሚታወቁበት ሃይማኖታዊነት፤ ሰብዓዊነት፤ ታጋሽነት፤ ሩህሩህነት ወዘተ የመሳሰሉትን ታላላቅ ባሕሪያት ፈጽሞ የተቃረነ መሆኑን ይገልጻል፡፡ “ሁሉም ያልፋል” የሚለውን ብሂል ፈጽሞ የዘነጉ፤ ጊዜያዊ የበላይነታቸውን እንደ ዘለዓለማዊነት አድርገው የቆጠሩ፤ በግፍ ያፈሰሱት ደም ጊዜው ይዘግይ እንጂ እንደሚፋረዳቸውና ተገቢውን ፍርድም እንደሚሰጣቸው መጽሐፉ ዋቤ ሰጥቶአል፡፡ ይኸውም ማንነቱን ቀይሮ አሜሪካ የገባው ፈለኝ ዓለሙ በዴኒቭር ኮሎራዶ ተይዞ  ከ36 ዓመታት በኋላ የተሰጠውን የ22 ዓመታት ፍርድ ስንመለከት ለሌሎችም ማስጠንቀቂያ ነው፡፡ አይሁዶችን የጨፈጨፉ የናዚ ሂትለር መንግሥት ሰዎችም እንዲሁ አላመለጡም፡
ከ1980 ዓ.ም በኋላ እና በኢሕአዴግ ዘመን የተወለደው ወጣት ትውልድ ከሞላ ጎደል የኢትዮዽያ ሕዝቦች ከድህነት፤ ከበሽታ፤ ከረሃብ ከብሔር ጭቆና ተላቀው ሕዝባዊና ዲሞክራሲያዊ መንግሥት ለመመስረት ስላደረጉት ትግል ባይተዋር ይመስላል፤ አለያም ስለ ተካሄደው ትግል እምብዛም አያውቅም ማለት ይቻላል፡፡ በመሆኑም አሁን ያለው ይህ ወጣት ትውልድ የቀደመው ያ ትውልድ ስለከፈለው መስዋዕትነት ከአቶ ነሲቡ ስብሀት መጽሐፍ ግንዛቤ እንዲወስድ ያስችለዋል፡፡ የዚህ ዘመን ወጣት ጉዳዩን መገንዘብ ብቻ ሳይሆን ይህንን የመሰለ ድርጊት በድጋሚ አንዳይከሰት የቀደመ ታሪኩን ማወቅ፤ መዘጋጀትና መጠንቀቅ ይገባዋል፡፡
ባለፉት 23 ዓመታት የተወለደው የአሁኑ ትውልድ ማንነቱንና ምንነቱን ወደፊትስ አቅጣጫው ምን መሆን እንዳለበት ከወዲሁ መገንዘብ የሚኖርበት ዘመን ላይ ተደርሷል፡፡ ታላቅ የነበረ ሕዝብ ወደ ጥንቱ የታላቅነቱ መሰረት እያመራ መሆኑን ማጤን ጊዜው አሁን ነው፡፡
በ1966 ዓ.ም አብዮት የዲሞክራሲ መብቶቹን ሊቀዳጀ የነበረ ሕዝብ  በወታደራዊው ደርግ መብቶቹን በመነጠቁ የተነሳ መብቱን ለማስመለስ የኢትዮዽያ ብሔር ብሔረሰብ ወጣቶች በቀጣይነት በየድርጅታቸው ረጅም ከገጠር የትጥቅ ትግልን ለማካሄድ ወስነው በከፈሉትን መስዋዕትነት ደርግን በ1983 ዓ.ም ከስልጣን ለማስወገድ በቅተዋል፡፡
በዚህ አጋጣሚ ለዚህ አስተያየት አንባቢዎች ለማሳወቅ የምፈልገው “ ኢሕአፓ እና ስፖርት ” እውነተኛ ታሪክ በሚል ርዕስ በገነነ መኩሪያ(ሊብሮ) 2005 ዓ.ም የተጻፈው መጽሐፍ አቶ ነሲቡ ያቀረቡትን መረጃ የሚያጠናክር ሆኖ አግንቼዋለሁ፡፡ ፈልገው ያንብቡት፡፡
ክንፈ ኪሩቤል ተስፋሚካኤል(አዲስ አበባ) ጥር 2007 ዓ.ም

No comments:

Post a Comment